26 Sep

ደመራ | መስቀል

የዛሬው በዓል የደመራ በዓል በመባል ይጠራል፡፡ የበዓሉ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን በዓሉ አገር አቀፋዊ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ በዓልም ነው፡፡

ወደ ኢየሩሳሌም ያመራችው ንግሥት ዕሌኒ ኢየሩሳሌም ደርሳ ስለ ነገረ መስቀሉ ስትመረምር ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ ሽማግሌ መስቀሉ ያለበትን እንዲህ ሲል ነግሯታል ‹‹ከሦስቱ ተራራዎች በአንዱ ነው ያለው ይባላል›› ብሏታል፡፡
እርሷም ሱባኤ ገብታ ስትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ ዕሌኒ ዕሌኒ ብሎ ጠርቶ በእራይ ነግሯት ካህናትን ሰብስባ ጸሎት እንድታስደርስ፣ ጸሎተ ዕጣን የተጸለየበት እጣን በመያዝ ደመራ ሠርታ በእሳት እንድትለኩሰው አዘዛት፡፡ የደመራውም ጭስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በዛሬው ዕለት መስከረም 16 ቀን አመለከታት፡፡
ከዚህ በኋላ መስከረም 17 ቀን ማስቆፈር ጀምራ መጋቢት 10 ቀን ከተቀበረበት አውጥታዋለች፡፡ መስቀሉ ሲወጣ እንደ ፀሐይ ዓለምን አበራ፡፡ አብሮ የተቀበረው ወንበዴዎቹ ተሰቅለውበት የነበረው መስቀልም ተገኝቷል፡፡ ግን ኃይል አልነበረውም፤ ዛሬም የጌታን መስቀልና የወንበዴዎቹን መስቀል መለየት ያስፈልጋል፡፡
መጋቢት 10 ቀን መስቀሉን ያገኘችው ንግሥት ዕሌኒ በኢየሩሳሌም ታላቅ ቤተ መቅደስ አሠርታ አስቀመጠችው፡፡ በዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ከመስቀሉ በረከትን ማግኘት ጀመሩ፡፡ ይህንን የተመለከቱ አሕዛብ(በመስቀሉ ያላመኑ) ክርስቲያኖች እንዳይድኑበት እንደ ቀድሞው እንደ አይሁድ አህዛብ የተባሉት ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው መቅደሱን ሰብረው መስቀሉን ዘርፈው ወሰዱት፡፡ ከዚህ በኋላ የቤዛንታይን ንጉሥ የነበረው ሕርቃል ምእመናን በጸሎት እና በምህላ እንዲረዱት ጠይቆ ወደ ፋርስ በመዝመት ድል አድርጎ መስቀሉን ይዞ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ መስቀሉም ለ714 ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ወደ ግሪክ ወስደው የዓለም ክርስቲያን ነገሥታት ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ የጌታችን ቀኝ እጅ ያረፈበት መስቀልም ለአፍሪካ ደረሰ፡፡ ከአፍሪካም ለግብጽ፡፡

እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገባ?

በኢትዮጵያ አጼ ዳዊት በነገሡበት ዘመን ግብጻውያን በክርስቲያኖች ላይ ሰልጥነው ግብጽ ሀገር አፍሪንጅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ጨፈጨፉ፡፡
አጼ ዳዊት ጭፍጨፋው ካላቆመ ወደ ግብጽ ወታደሮችን እንደሚያዘምቱና የዓባይን ወንዝም እንደሚገድቡባቸው ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ በዚህ ጊዜ የግብጽ መንግሥት ዲፒሎማቶቹን የወርቅ፣ የብርና የዝሆን ጥርስ ሌሎችንም ገጸ በረከቶች በማስያዝ አጼ ዳዊትን እንዲማፀኑ ላካቸው፡፡
አጼ ዳዊትም ወርቅና ብር እንደማይፈልጉ የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ እንዲቆም ነገር ግን ግብጽ የተቀመጠውን ግማደ መስቀልና ቅዱስ ሉቃስ የሳላትን የእመቤታችንን ስዕለ አድኅኖ እንደሚፈልጉ ነግረው መለሷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግማደ መስቀሉን እና የእመቤታችንን ቅዱስ ሉቃስ የሳላትን ምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል ከግብጽ ተረከቡ፡፡ እሳቸውም በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ልዩ ስሙ ስናር ከሚባል ቦታ ሲደርሱ መንገድ ላይ አርፈዋል፡፡ ልጃቸው አጼ ዘርአያዕቆብም መስቀሉን ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል›› በተባሉት መሠረት በዳግማዊት ጎልጎታ ግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጠውታል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል አጀማመር
ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታ የደመራ ዕንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው፡፡
መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።
ይህ ዕለት ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡
በዓለ መስቀል፣ በክርስትና ሃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ማስታወሻ በዓል ሲሆን በምዕራብም በምስራቅም አብያተ ክርስቲያናት ይሄንን መታሰቢያ መስከረም 3 ቀን ሲያከብሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ታከብራለች።


ትምህርት
በመስቀሉ ድነናል ፤(ኤፌ 1÷7 ፤ 1ኛጴጥ1÷19)
በመስቀሉ ክርስቶስ ወደ ራሱ አቅርቦናል፤ (የሐ 12÷32)
በመስቀሉ ሠላምን አግኝተናል፤ (ሮሜ 5÷10፣ ቆላ 1÷20)
በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ጽድቅን ቅድስናን እና ቤዛነትን አግኝተናል (ሮሜ5÷2 ፣1ኛቆሮ 1÷31፤ ዕብ 10÷10)፤
በመስቀሉ የእዳ ደብዳቤያችን ተደምስሷል፡፡ (ቆላ.2÷14)
በመስቀሉ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ለመግባት ሞገስን አግኝተናል (ዕብ.10÷19)
መስቀል ኃይላችን እና መመኪያችን እንደሆነ ተረድተናል፡፡
ስለ እኛ በመስቀል ላይ መከራ የተቀበለውን የክርስቶስን ፍለጋ መከተል፤(1ኛጴጥ.1÷20)
የተሰቀለውን ክርስቶስን መስበክ፤(1ኛቆሮ.1÷23)
ሞቱን እስከ ዳግም ምፅዓት ማወጅ፤ (1ኛቆሮ.11÷26)
በመስቀሉ ላይ ለድኅነት የፈሰሰውን ቅዱስ ምስጢር በእምነት መቀበል ከኛ ይፈለጋል፤ (ማር.14÷22)

መልእክት
የመስቀሉ ነገር በብዙዎች ዘንድ የጥበብ ተቃራኒ የሆነ ሞኝነትን መስሎ መሰናክል ሆኗል፡፡ ለሚያምኑት ግን የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ ነው፡፡ ዓለም በጥበቡና በዕውቀቱ፣ በኀይሉም አልዳነም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የዓለምን ኀይል፣ ጥበብና ዕውቀት ሞኝነት በመሰለው በመስቀል ነገር ከንቱ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም በድካምና በሞኝነት ማለት በመስቀል ስብከትና በእምነት ዓለምን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ስለ መስቀልና በመስቀል ስለተሰቀለው ክርስቶስ መሰበክ በማያምኑት ዘንድ ሞኝነት፣ ድካምና መሰናክል ቢመስልም በምእመናን ዘንድ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ሆኖ ይታያል፡፡ ምክንያቱም በሰው ዘንድ ሞኝነት ሆኖ የታየው የእግዚአብሔር ሥራ ከሰው ጥበብ ይልቅ ስለሚጠበብ ነው፡፡ በሰው ዘንድ ድካም ሆኖ የታየው የእግዚአብሔር ሥራም ከሰው ኀይል ይልቅ ስለሚበረታ ነው፡፡ እንግዲህ ቅዱስ መስቀል በሚያምኑና በማያምኑ መካከል መለያ ምልክት ነው፤ መለኪያ ሚዛንም ነው፡፡ ለእኛ ለምናምን ቅዱስ መስቀል ወደ ሰማይ የምንደርስበት መሰላል ነው፡፡ ለማያት ይፈልጋል ግን ወደ ሰማይ እንዳይደርሱ የሚሰናከሉበት እንቅፋት ነው፡፡
በክርስቶስ አምናለሁ የሚል ሁሉ እንደ አይሁድ «መስቀሉን አይግፋ» ነገር ግን እንደ ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ይፈልግ፤ መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነውና፡፡
እግዚአብሔር በመስቀሉ ኃይል ይጠብቀን፡፡ አሜን!!

መልአከ ብሥራት ቀሲስ አዲሱ ላቀው የሜሪላንድ ደብረ ብሥራት ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ